Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ለውጥ አምጥታለች – የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የግብርና ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ለውጥ ማምጣቷን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የግብርና ሚኒስትር ግሪጎር ሙታሻል ገለጹ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የግብርና ሚኒስትር ግሪጎር ሙታሻል ጋር ኢትዮጵያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በግብርናው ዘርፍ በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)÷ አፍሪካ ለግብርና ልማት ምቹ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖራትም የአፍሪካ ሀገራት ግን ህዝባቸውን በአግባቡ መመገብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም ፥ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የግብርና ሚኒስትር ግሪጎር ሙታሻል በበኩላቸው ፥ በግብርናው ዘርፍ በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ እውቅና ሰጥተዋል፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰም እንደሚፈልግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በግብርናው ዘርፍ ልምድ ለማካፈል ያላትን ፈቃደኝነት የገለጹት ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ፥ በቀጣይ በጋራ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሚኒስትሮቹ ተወያይተው ተግባብተዋል፡፡

Exit mobile version