የሀገር ውስጥ ዜና

የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ሰፊ አለም አቀፍ ግንኙነት መፍጠር የቻለችበት መድረክ መሆኑ ተገለፀ

By Feven Bishaw

November 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ሰፊ አለም አቀፍ ግንኙነት መፍጠር የቻለችበት መድረክ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ÷የአባል ሀገራት አምባሳደሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በካዛን በተካሄደው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ውጤቶች እና በካዛን ቃልኪዳን ቀጣይ ትግበራ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን÷ 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ አባል ሀገራት ቀጣይ ትብብራቸውን ማስፋት በሚችሉባቸው እንዲሁም ተጨማሪ አባላት ወደ ስብስቡ ወደሚቀላቀሉባቸው መንገዶች ዙሪያ ውጤታማ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳይ ላይ በትብብር ለመስራት እና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቋም በግልፅ ማሳየት መቻሏ በብሪክስ 2024 ጉባኤ ውጤታማ የነበረች ሀገር አድርጓታል ያሉት አምባሳደሩ ÷ከጉባኤው ጎን ለጎን በጤና፣ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ እና በንግድ ትብብር ላይ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋርም ሰፊ ውይይቶች በማድረግ ስምምነት ላይ መድረሷን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ያላት ተሳትፎ እና ትብብር አባል ሀገራቱ ለያዙት አላማ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚጫወት አምባሳደሩ አመልክተዋል፡፡

ብሪክስ ከተሳትፎም በላይ ነው ያሉት አምባሳደሩ ÷ኢትዮጵያም የብሪክስ አባል አገር በመሆኗ ከምጣኔ ሃብታዊ እድገት ባልተናነሰ በቀጣናው የፖለቲካና እና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር ግንኙነቷን እንዲሁም ለህብረቱ ግቦች መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለች ብለዋል፡፡

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ጥቅምት ወር ማገባደጃ ላይ በሩሲያ ካዛን ከተማ ለሶስት ቀናት የተካሄው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ፍትሃዊ የአለም ስርዓትን መፍጠር የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እና የካዛን ቃልኪዳንን በማጽደቅ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በጸጋ ታሪኩ