የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

By ዮሐንስ ደርበው

November 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጫና የሚቀንስና ካፒታሉን ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)÷ የልማት ድርጅቶች ከንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር ባለመመለሳቸውና የብድር ወለዱም በጣም ከፍ በማለቱ በባንኩ ላይ ጫና መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

ባንኩ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቋም በመሆኑ 900 ቢሊየን ብሩ የመንግሥት ዕዳ ሠነድ ሆኖ እንዲከፈል እና መነሻ ካፒታሉም ከፍ እንዲል ውሳኔ ላይ ተደርሷል ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላም የመንግሥት ዕዳ ሠነድ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1346/2017 ሆኖ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡