Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቻይና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት በቀጣይም በኢትዮጵያ ከሚገኙ የግል እና የመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በቻይና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ልዑክ ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የኢትዮ-ቻይና ኢንቨስትመንት አጋርነት ጠንካራ መሆኑን አምባሳደር ምስጋኑ ጠቁመዋል።

የቻይና ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ እየተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ ፋይዳ በመነሳት ተጨባጭ የቢዝነስ ትስስር እንዲፈጠር መንግስት ተጨማሪ እድሎች እንዲፈጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቻይና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ልዑክ ቡድን መሪ ጆን ጂልስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በሰፊው የሚገኙባት በመሆኗ የኢንቨስትመንት ትስስርን የበለጠ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ ለቻይና ኩባንያዎች የምታደርገው እገዛ እና የፖሊሲ ድጋፍ አድንቀዋል።

በቀጣይም በኢትዮጵያ ከሚገኙ የግል እና የመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version