አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋራ ጥረቶቻችን ረሃብን በማጥፋት ለሁሉም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ርብርብ ፍሬ እንዲያፈራ እንደሚያስችሉ ተስፋ አለኝ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የ’ከረሃብ ነጻ ዓለም’ ጉባኤ ተሳታፊዎችን እንኳን ወደ አፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና በሰላም መጣችሁ ብለዋል።
ዓለም አቀፍ መሪዎችን፣ ባለሞያዎችን እና የጉዳዩ ተቆርቋሪዎችን በአንድ ላይ በማምጣት እንዲወያዩ በማድረግ የጋራ ጥረቶቻችን ረሃብን በማጥፋት ለሁሉም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ርብርብ ፍሬ እንዲያፈራ እንደሚያስችሉ ተስፋ አለኝ ሲሉም መልዕክታቸውን አስፍረዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ሽግግርና ምርታማነት ላይ በማተኮር የሠራነው ሥራ የታረሰ መሬታችን እጥፍ በማድረስ ከፍ ያለ እሴት ባላቸው የኢንዱስትሪ አዝዕርት ምርት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አስገኝቷልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፥ በሚቀጥሉት ቀናት የጉባኤው ውይይቶች የጋራ ግቦቻችን ስኬት የሚያፋጥኑ ታላላቅ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እተማመናለሁ ነው ያሉት።