የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ-እስራኤል ኢኖቬሽን ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች መካሄድ ጀመረ

By Shambel Mihret

November 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው የኢትዮ-እስራኤል ኢኖቬሽን ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች መካሄድ ጀምሯል፡፡

ዝግጅቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስክ በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ያለውን ፈጠራ እና ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ ሲሆን ለአራት ቀናት እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ በአዲስ የፈጠራ ዘመን ላይ እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡

የእስራኤል የፈጠራ ሞዴል ለኢትዮጵያ ትምህርት ሰጭ በመሆኑ የትብብር ማዕቀፍ በመመሥረት÷ በጋራ ሐሳቦች የሚያብቡበት፣ ስታርትአፖች የሚበለፅጉበት፣ ቴክኖሎጂ ለኢኮኖሚ ልማት ማበረታቻ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር እንችላለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቫራሃም ንጉሴ በበኩላቸው÷ በዓለም ላይ ስኬታማና ግንባር ቀደም የፈጠራ እና ስታርትአፖ ሥነ-ምኅዳርን በማቋቋም ሀገራቸው ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያጋሩ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብትና በሰው ኃይል የታደለች መሆኗን ጠቅሰው÷ ሀብቱን በቴክኖሎጂ እና በኢኖቬሽን በመደገፍ ለኢኮኖሚ እድገት ለመጠቀም የሚደረገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምታግዝ መናገራቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡