አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በብሪታኒያ ግላስኮ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 92ኛው የኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
በጉባዔው ላይ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዑክ እየተሳተፈ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ጨምሮ የድርጅቱ አባል ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የተለያዩ ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር በጉባዔው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ የድርጅቱ አባል ሀገራት ለዓለም ሰላም መስፈን በትብብር በመሥራት እያደረጉ ያሉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ሀገራቸውም ለኢንተርፖል እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
በጉባዔው ላይ ያለፈው ዓመት የድርጅቱ ሥራ አፈፃጸም፣ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት ውይይት ከተደረገ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ኢትዮጵያ የድርጅቱን ዓመታዊ ጉባዔ የማዘጋጀት ዕድል እንዲሰጣት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን÷ የድርጅቱ ኃላፊዎችም በቀጣይ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ እንደሚያመቻቹ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልዑክ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡