ቢዝነስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 አውሮፕላን ከኤር ባስ ተረከበ

By Mikias Ayele

November 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 “Ethiopia land of origins” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የመንገደኞች አውሮፕላን ዛሬ ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያ ተረክቧል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወቃል።

ከዚህ ባለፈም አየር መንገዱ በዓመት እስከ 130 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩ አንስተዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ባለቤት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው ተቋምም ያደርገዋል።

አየር መንገዱ በዛሬው ዕለትም የኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላንን ተረክቧል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌ/ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ለሚክ የኤር ባስ ኩባንያ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በዚህ ወቅት ÷ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ላይ መሆኗን አንስተዋል።

በአፍሪካ የመሪነት ሚናውን ድርሻ እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷ ኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ዛሬ ከኤር ባስ ኩባንያ የተረከበውና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ 350_1000 አውሮፕላንም ለአየር መንገዱ ቀጣይ እድገት ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷የኤ350-1000 አውሮፕላን ወደ ገበያው መግባት አየር መንገዱ የተያያዘውን ፈጣን እድገት በላቀ ደረጃ ለማሳለጥ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስገባት ፈር ቀዳጅ መሆኑን በማንሳት÷ ኤ 350-1000 አውሮፕላንም በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቅ ስኬት መሆኑን አክለዋል።

የኤር ባስ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ውተር ቫን ዌርሰች÷ ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350-1000 አውሮፕላን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 ስኬት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል ።

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመስራት ትልቅ ፍላጎት አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።