Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጀርመን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከጀርመን የምግብና እርሻ ሚኒስትር ቼም አዝደሚር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ሀገራቱ በግብርና ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች እንዲሁም በአውሮፓ ህብረት የደን ጥበቃ አዋጅ ዙሪያ መክረዋል፡፡

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያና ጀርመን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ጀርመን በግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ  እውቅና ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ቡናን በተመለከተ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ኢትዮጵያ ከጀርመኑ የልማት ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ጋር በመተባበር መመሪያውን ተግበራዊ ለማድረግ ሥራ መጀመሯን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን መመናመንን እንደቀነሰች የገለፁት ሚኒሰትሩ÷መርሐ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ቼም አዝደሚር በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ማገዘ በሚቻልበትና በአዲሱ የአውሮፓ ሕብረት ሕግ ዙሪያ በስፋት መምከራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አውሮፓ ህብረት ያወጣውን ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ  የጀመረችውን ሥራም ሚኒስትሩ አድንቀዋል።

ሀገራቸው ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጥረት እንዲሁም የአረንጓዴ ሽግግርን በሙሉ አቅሟ እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

በመራኦል ከድር

Exit mobile version