አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የሃይማኖት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን የሃይማኖት መከባበርና አብሮነት የሚያሳይ የስዕል ኤግዚቢሽን ተከፈተ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የረጅም ዘመናት የሃይማኖት መከባበርና አብሮነት ለዓለም ለማሣየትና ለማስገንዘብ ያለመ የስዕል ኢግዚቢሽን ተዘጋጅቷል።
የስዕል ኢግዚቢሽኑ በፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ በሰላም ሚኒስቴር አቶ ብናልፍ አንዱአለም እና በሐይማኖት አባቶች ተመርቆ መከፈቱን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የሃይማኖቶች አባቶች፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምስራቅ አፍሪካ፣ የሩሲያ፣ የሞሮኮና የደቡብ አፍሪካ የሃይማኖት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በኮንፈረንሱ ላይ እየተሳተፉ ነው።