አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ምርጫ ለሀገሪቱ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ግምት ተሰጥቶት የብዙዎችን ትኩረት ይስባል።
ሰዓታት የቀሩት የአሜሪካ ምርጫ ካማላ ሀሪስና የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብርቱ ፉክክር እያደረጉበት ነው።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሀሪስ ለምርጫ ይረዳቸው ዘንድ የምረጡኝ ቅስቃሳ ሲያደርጉ ከርመዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ለድጋሚ ፕሬዚዳንትነት ምረጡኝ እንቅስቃሴያቸው ላይ የግድያ ሙከራ ሁለት ጊዜ ተደርጎባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡
ካማላ ሀሪስ በበኩላቸው በተለያዩ ግዛቶች ቅስቀሳቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
ሁለቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች ማለትም ሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክ ውስጥ እጩዎች መነሻቸውን በማድረግ ይወዳደራሉ፡፡ ከዚያ ውጭም በግላቸው የሚወዳደሩ እጩዎችም ይኖራሉ፡፡
ዴሞክራቶች የሊበራል ፖለቲካ ፓርቲ ናቸው፤ አጀንዳቸው በዋናነት የሲቪል መብት መከበር፣ ሰፊ የማህበራዊ ደህንነት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡
ሪፐብሊካኖች ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ፓርቲ ናቸው ይባላል ጂኦፒ ወይም ግራንድ ኦልድ ፓርቲ በመባልም ይታወቃሉ፡፡
የጦር መሳሪያ ላይ ህጎችን በማጥበቅ እንዲሁም የታክስ መጠንን መቀነስ እንዲሁም በኢሚግሬሽን ላይ ህጎችን ማጥበቅ ፓርቲው የቆመላቸው አጀንዳዎቹ ናቸው፡፡
ብዙውን ጊዜ አሸናፊው የሚታወቀው በምርጫው ምሽት ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2020 ግን ሁሉንም ድምጽ ለመቁጠር ጥቂት ቀናት ፈጅቷል።
የፕሬዚዳንት ለውጥ ካለ ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ ሽግግር በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህም አዲሱ አስተዳደር የካቢኔ ሚኒስትሮችን ለመሾም እና ለአዲሱ የስራ ዘመን እቅድ ለማውጣት ጊዜ ይሰጣል።