አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት ያገኙ እናቶችን 74 በመቶ ማድረስ መቻሉን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለፁ፡፡
የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀትን ለማጠናከር ያለመ ውይይት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የሁለቱም ሴክተሮችና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነዉ፡፡
በመድረኩ የጤና ሚኒስትሯ÷ የሴቶችና ህጻናት ጤናን ለማሻሻል እየተሰራ ያለዉን ስራ አብራርተው÷ በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት ያገኙ እናቶችን 74 በመቶ ማድረስ መቻሉ ጥሩ እምርታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የቤተሰብ ጤና ልማትን እንደ ዋና ስትራቴጂክ ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ጤንነቱ የተጠበቀና አምራች ዜጋ እንዲኖር በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸዉ÷ የእናቶችና ህጻናት ፣የወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን ጤና በሚፈለገዉ ልክ ለማሻሻል በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀትን እንደገና ለማጠናከር የሚረዳ ሀገር አቀፍ መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ይህንን ለመተግበር የንቅናቄ መድረክ እንደሚካሄድና በዚህም የተያዘዉን እቅድ ለማሳካት በየደረጃዉ ያለዉ አመራርና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡