የሀገር ውስጥ ዜና

የኃይማኖት ተቋማት ፅንፈኝነትና የመከፋፈል እሳቤን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

By Melaku Gedif

November 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኃይማኖት ተቋማት ለዓለም ፈተና እየሆነ ያለውን የፅንፈኝነትና የመከፋፈል እሳቤን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር በተባባሩት አረብ ኢምሬቶች ከሚገኘው ከመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው ።

በጉባኤው ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ጨምሮ የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ዶክተር ካልፍ ሙባረክ፣ የሃይማኖቶች አባቶች ፣የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ በኃይማኖትና በሰላም ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል።

እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ፣ የሩሲያ፣ የሞሮኮ እና የደቡብ አፍሪካ የሃይማኖት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በወቅቱ እንዳሉት፤ የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት በማጠናከረ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው።

ኢትዮጵያ ብዝሃ ኃይማኖቶች በጋራ ተቻችለው የሚኖሩባት በመሆኑ ለዓለም ትልቅ ምሳሌ እንደሆነች አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ የፅንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ አብሮ ለመኖር አደጋ እየሆነ መምጣቱን ተናግረው፤ የኃይማኖት ተቋማት ለአብሮነትና መቻቻል አደጋ የሆነው የፅንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ ለማስወገድ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል።

በጉባኤው የኃይማኖት ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩበት፣ የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መምከር እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በማስፈን ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው፤ አሁን ላይ በዓለም ላይ እያጋጠሙ ያሉ የመከፋፈል ችግሮች ለመፍታት የኃይማኖት ተቋማት የመቻቻል ትርክትን መገንባት ላይ መስራት አለባቸው ብለዋል።

የኃይማኖት መሪዎች እና ተቋማት በተለያዩ እምነቶች መካከል ውይይት እና መግባባትን መፍጠር፣ የተዛባ አመለካከትን ማፍረስ እና መከባበርን ማጎልበት ላይ አበክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።