Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የውኃ ሀብታችንን በብቃት ስንመራ የጎረቤት ሀገራትን ጭምር ብልጽግና የምንደግፍበት ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውኃ ሀብታችንን ስንጠብቅና በብቃት ስንመራ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገራትን ጭምር መረጋጋትና ብልጽግና የምንደግፍበት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

 

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ የሃድሮሜት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

 

በጉባዔው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር÷ ዓለምን እየፈተነ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ሳይሆን የቅድመ መከላከልና ማስጠንቀቂያ ሥራ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡

 

ለዚህ ደግሞ በሳይንስና ምርምር የተደገፈ ፈጣን ምላሽ እንደሚጠበቅም በአጽንዖት ገልጸዋል።

 

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ ለመቀልበስ ከመቼውም ጊዜ በተለየ በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝ በመግለጽ÷ ለአብነትም በአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፍ እየተገበረች ያለውን ሥራ አብራርተዋል፡፡

 

የአየር ንብረት ችግርን ለመቋቋምና የውኃ ሐብትን በብቃት ለማሥተዳደር የምታደርገው ሥራም ከራሷ የተሻገረና ወንዞቿ የሚያቋርጧቸው የጎረቤት ሀገራትን ጭምር ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

 

በተሠራው ተፈጥሮን የማስተካከል ተግባርም በወንዞችና በውኃ ተፋሰሶች አመርቂ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለአብነትም የከርሰ ምድር ውኃ መጨመርና የጎርፍ ተጋላጭነት መቀነስ የታዩ ለውጦች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 

‘የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነትና የቀጣናው የውሃ ሀብት አሥተዳደር አስፈላጊነት’ በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባዔ ላይ÷ የአየር ንብረት ለውጥና የውሃ ሃብትን በሚመለከት ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ።

 

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የሀገር ውስጥ፣ ከአፍሪካ ሀገራት፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ከሕንድ የመጡ የዘርፉ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

 

በፍሬሕይወት ሰፊው

Exit mobile version