አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች በገጠሙት የፀጥታ ችግሮች ዙሪያ የሚመክር የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በደባርቅ ከተማ ወቅታዊውን የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት ከከተማው ወጣቶች ጋር ውይይት እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የከተማው ወጣቶች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ በአይከል ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሰላም ኮንፈረንስ ከሁለቱ ጭልጋ ወረዳና ከአይከል ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ምሁራንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በስናን ወረዳ የደብረ ዘይት ቀበሌ ነዋሪዎች በወቅታዊ ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ እንደሚገኙ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም በግንደወይን፣ በቻግኒ፣ በምድረ ገነት፣ በገረገራና መተማ ዮሐንስ ከተሞች ”ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በኮንፈረንሱ የከተሞቹ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሙያ ማህበራት፣ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤት አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።