አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ በገቢ ረሱ ሐንሩካ ወረዳ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በሀንሩካ ወረዳ እየለማ የሚገኘውን የሙዝ ማሳ ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
አቶ አወል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አሁን ለገበያ እየቀረበ ያለው የሙዝ ምርት ከተሠራ የማይቻል እንደሌላ በእውን ያሳየንበት ነው ብለዋል።
ለገበያ የደረሰውየሙዝ ምርት ባለፈው ዓመት የተተከለ መሆኑን ጠቅሰው÷ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት ለውጤት መብቃቱን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የልማት ሥራው ለክልሉ ብሎም ለኢትዮጵያ ባለሃብቶች ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ አወል አርባ በገቢ ረሱ አሚባራ ወረዳ በሲዲሃፋጌ እየተከናወኑ የሚገኙትን የልማት ሥራዎች መጎብኘታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡