የሀገር ውስጥ ዜና

ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የተፈፀመበት 4ኛ ዓመት ታስቦ ዋለ

By Mikias Ayele

November 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የተፈፀመበት 4ኛ ዓመት በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ታስቦ ዋለ።

“እንዳይደገም ሁሌም እንዘክረዋለን” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘከረው በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሰሜን ዕዝ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ እውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና ሕይወቱን ሳይሰስት ስለመስጠቱ ተነስቷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት ሥነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን፤ ለሕዝብና ለሀገር ዋጋ ሲከፍል በኖረው ሠራዊት ላይ የተፈፀመው ጥቃት በፍጹም የማይገባ ተግባር እንደነበር ገልፀዋል።

በዕዙ ላይ ጥቃት የተፈፀመበት ቀን የሚዘከረው ትውልዱ እንዲማርና እንዳይደገም ለማስታወስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተፈተነ ቁጥር የሚጀግነው ሠራዊታችን በፈተናዎች ሁሉ እየፀና የሀገርና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ተግባሩን ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የመቻል ስፖርት ክለብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን በበኩላቸው፤ ዝክረ-ሰሜን ዕዝ በሠራዊታችን ላይ የተፈፀመው ጥቃት እንዳይደገም የማድረግ ዓላማን የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰሜን ዕዝን ለመዘከር የተሳተፉ የሠራዊት አባላት፤ የተፈፀመው የጭካኔ ተግባር የማይረሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጀግኖች ሰማዕታትን ሁሌም ስንዘክራቸው እንኖራለን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በእለቱ ወቅቱን የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ የቀረበ ሲሆን፤ የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓትም ተከናውኗል።