የሀገር ውስጥ ዜና

 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተወካዮች አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ አስረከቡ

By Mikias Ayele

November 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባለድርሻ አካላትና የማህበረሰብ ተወካዮች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲቀርብ የለዩአቸውን አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከቡ።

በኮሚሽኑ አስተባባሪነት በክልሉ ከጥቅምት 18 ቀን 2017 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፤ ከ1 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልሉ መንግስት፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና የልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

የባለድርሻ አካላቱ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችን በውይይት ለይተውና አደራጅተው ዛሬ ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።

የክልሉን አጀንዳዎች የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር ) እና ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር ) ከተወካዮቹ ተቀብለዋል።

በኢብራሂም ባዲ