የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የቱሪዝም ልማትን ማነቃቃት እደሚገባ ተጠቆመ

By Mikias Ayele

November 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ልማት ለማነቃቃት መስራት እደሚገባ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ፡፡

32ኛው ክልላዊ የቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በደብረብርሃን ከተማ ተከብሯል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ÷ የአማራ ክልል ዕምቅ የቱሪዝም አቅም ቢኖረውም በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ አመላክተዋል።

ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን አሁን ላይ መንግስት የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት የጀመረውን ስራ በመደገፍ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ማህበረሰቡ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የቱሪዝም ቀንን ስናከብርም በአማራ ክልል ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሰው ሰራሽ ችግሮች የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ልማት ለማነቃቃት የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም ለ45ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ37ኛ ጊዜ እንዲሁም በአማራ ክልል ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በአበበ የሸዋልዑል