የሀገር ውስጥ ዜና

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዲሰበሰብ ጥሪ ቀረበ

By amele Demisew

November 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዲሰበሰብ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጥቅምም ጉዳትም እንዳለው አስገንዝበዋል።

የመኸር አዝመራ በደረሰባቸው እና ሰብል መሰብሰብ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ጉዳት ሊያደርስ እንሚችልም አሳስበዋል፡፡

በነዚህ አካባቢዎች ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ሰብሉ ጉዳት እና ብክነት ሳይደርስበት በወቅቱ መሰብሰብ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህም ዘመቻ “ሰብል መሰብሰብ” በማወጅ በንቅናቄ ሰብሉን በወቅትና በጊዜ መሰብሰብ እንሚደባ ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ሙያተኞች፣ ሠራተኞች፣ የፀጥታ አካላት፣ ተማሪዎች፣ አርሶአደሮች ተቀናጅተው መረባረብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ባለሙያዎች የሚሰጡትን የጥንቃቄ ምክሮችንም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ሰብል ገና ባልደረሰባቸው፣ የመጀመሪያውን ዙር የበልግ አዝመራ በሚካሄድበት፣ የበጋ መስኖ በተጀመረበት አካባቢ ደግሞ እየጣለ የሚገኘውን ዝናብ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ዕቅድ ከግብ የሚደርሰው የሚያጋጥሙንን ሁሉንም ችግሮች በተባበረ መንገድ በመሻገር፣ መልካም አጋጣሚዎችን ደግሞ አሟጠን መጠቀም ስንችል ነው ብለዋል።