የሀገር ውስጥ ዜና

ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ 44 ከባድ ተሸከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገባ

By amele Demisew

November 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በሦስተኛ ዙር 44 ገልባጭ ከባድ ተሸከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱ ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ወደሀገር ውስጥ እያስገባቸው ከሚገኙት 330 ገልባጭና የጭነት ከባድ ተሸከርካሪዎች መካከል በመጀመሪያ ዙር 36፣ በሁለተኛው ዙር 30 ተሸከርካሪዎችን በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

በሦስተኛ ዙር ደግሞ 44 ተጨማሪ ገልባጭ ከባድ ተሸከርካሪዎች ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ከባድ ተሽከርካሪዎች የሲሚንቶ ምርት ግብዓት የሆነውን ማዕድን ከማምረቻ ጣቢያው ማከማቻ ቦታ የሚያጓጉዙ እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ የሆኑ ገልባጭ ከባድ ተሸከርካሪዎች መሆናቸውን የደብረብርሃን ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ከጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።