Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል ከ11 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ11 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 146 የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ወረዳ የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተቋም ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወሳል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኩኑዝ አህመድ እንዳሉት ፥ የንጹህ መጠጥ ውሀ ችግር በዋናነት ጎልቶ ከሚታይባቸው የክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተለይም የሀረርጌ፣ ባሌ እና ቦረና ዞን ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህ ዓመትም በ11 ቢሊየን ብር የክልሉ መንግስት በጀት 146 የውሀ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን ፥ የጥልቅ እና መካከለኛ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ ምንጭ ማጎልበትያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከመንግስት በጀት በተጨማሪ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ8 ሺህ በላይ አነስተኛ ንጹህ መጠጥ ውሀ ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የውሃ ተቋማቱ ግንባታቸው ሲጠናቀቅም በአመዛኙ በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኝ ከሁለት ሚሊየን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

ይህም የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሀ ሽፋን አሁን ካለበት ከ87 ከመቶ ወደ 89 ከመቶ እንደሚያድግ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

Exit mobile version