ስፓርት

በፕሪሚየር ሊጉ ማንቼስተር ሲቲ ሲሸነፍ ሊቨርፑል አሸነፈ

By Melaku Gedif

November 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ10ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ማንቼስተር ሲቲ ሲሸነፍ ሊቨርፑል ድል ቀንቶታል፡፡

ወደ ቫይታሊቲ ስታዲየም ያቀናው የሊጉ መሪ ማንቼስተር ሲቲ በቦርንማውዝ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡

ለቦርንማውዝ ግቦቹን ሴሜኞ እና ኢቫኒልሰን ሲያስቆጥሩ÷ጆስኮ ግቫርዲዮል ደግሞ ሲቲን ከሽንፈት ያልታደገችዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ከመመራት ተነስቶ ብራይተንን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ÷ኮዲ ጋክፖ እና ሞሃመድ ሳላህ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ ሌሎች መርሐ ግብሮች ኢፕስዊች ታውን ከሌስተር ሲቲ 1 ለ 1 ሲለያዩ÷ ኖቲንግሃም ፎረስት ዌስትሃም ዩናይትድን 3 ለ 0፣ ሳውዝሃምፕተን ኤቨርተንን 1 ለ 0 አሸንፈዋል፡፡

የሊጉ መርሐ ግብር ሲቀጥል ምሽት 2:30 ላይ ዎልቭስ ከክሪስታል ፓላስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡