Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብልጽግና ፓርቲና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ዙሪያ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በቻይና ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የተካተቱበት የልዑካን ቡድን ጋር በቻይና ያደረግነው ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡

በቆይታቸው የኢትጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሚያስችል መልኩ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ስላለው የፓርቲ ለፓርቲ፣ የመንግስት ለመንግስትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ዙሪያ ሰፋ ያሉ ውጤታማ ምክክሮች ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች፣ የመስክ ጉብኝቶችና የተሞክሮ ልውውጥ መድረኮች በሀገር በቀል እሳቤ ሀገረ መንግስቶቻችንን የማፅናት ስራ ማጠናከር፣ በመሪዎች የተደረሰውን የኢትዮጵያና የቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ ትብብር ትግበራን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መስራት ላይ ውይይት መካሄዱንም ጠቅሰዋል፡፡

በሁለንተናዊ መልኩ የመበልፀግ ፍላጎትን ለማሳካት በቀጣይነት በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ መደጋገፍ በቆይታችን ልዩ ስፍራ አግኝቷል ሲሉም ገልጸዋል።

ከፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት አኳያ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጋር የአቅም ግንባታን ጨምሮ በአጠቃላይ በጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ዙሪያ የበለጠ ትብብርን ለማጠናከር ከስምምነት መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

ልዑኩ በቻይና ያደረገው ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት አቶ አደም ፋራህ÷ በቀጣይ የሁለቱ ሀገራትን ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት እና የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ለማጠናከር ጥረታችን አጠናክረን እንደምንቀጥል ብለዋል፡፡

Exit mobile version