አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመረጃ የበላይነት የያዘ ሃይልና ሀገር በሌሎች ሁኔታዎች ላይ የበላይነት የመያዝና የማሸነፍ እድሉ ሰፊ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በማስተርስ መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ም/ጠ/ሚ ተመስገን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በአሁኑ ወቅት ቀዳሚ እና ከፍተኛ ትግል የሚደረገው በመረጃ የበላይነት መያዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመረጃን አቅምና ጥቅም በአግባቡ የተገነዘበውና በ2010 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጣው የኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራር በደኅንነት ዘርፉ ላይ “ጫወታ ቀያሪ” የሆነ ሪፎርም እንዲካሔድ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
የዛሬው የተማሪዎች ምረቃ ከዚሁ ከሪፎርምና በቀጣይነት በማያቋርጥና ፈጣን የሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት ምህዳር ለወጥ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበርን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው÷ ዘርፉ ጊዜውን በሚመጥን ትምህርት ሊደገፍ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጠንካራ፣ አካታች፣ ብቁና ትውልድን ተሻጋሪ የመረጃና ደህንነት ባለሙያ ማፍራት ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ ለዚህም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ ሃላፊነትና ርዕዩን ለማሳካት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት የአቅም ግንባታ ማዕከል የሆነው የብሔራዊ ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በማስተርስ ደረጃ በ3 የትምህርት ፕሮግራሞች ለ2 ዓመታት ያስለጠናቸውን ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
ላለፉት 40 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ባለሙያዎችን ሲያሰለጥን የቆየው ተቋሙ ከጥር 2016 .ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማደግ በመረጃ ጥናትና ትንተና፣ በደኅንነት፣ የስነ-ልቦና ጥቃትን በመከላከል እንዲሁም በሳይበር ደህንነት ብቁ አመራሮችንና ባለሙያዎች እያፈራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው