አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከለማው ሰብል እስካሁን 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ በሪሶ ፈይሳ እንደገለጹት÷ በክልሉ የመኸር እርሻ 10 ነጥብ 85 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡
ከዚህም 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው÷ እስካሁን 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ መታረሱን የገለጹት ም/ሃላፊው ÷በክልሉ የመኸር ግብርና ሥራ በተቀናጀና በተሳካ መልኩ መከናወኑን ጠመቁዋል።
በግብርና ግብዓት አቅርቦት በቂ የማዳበሪያና ሌሎችም ግብዓቶች ተሟልተው ለመኸር እርሻው መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በበጋው የመስኖ ልማት ሥራ 4 ሚሊየን ሄክታር ምርት ለማልማት ዕቅድ መያዙን ገልጸው÷ ከዚህም ውስጥ አንድ ሚሊየን የማሳ ዝግጅት እንደተደረገ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሌላ በኩል እስከ አሁን 600 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑን ነው ያስረዱት፡፡