አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ነገ የአጀንዳ ማሰባሳብ መርሐ ግብሩን እንደሚጀምር አስታወቀ።
ከጥቅምት 24 እስከ 30 ቀን 2017ዓ.ም በሚቆየው በዚህ አጀንዳ የማሰባሰብ እና ውይይት ላይ ከ2 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሏል።
በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 57 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች በኮሚሽኑ የተለዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ ሀገር አቀፍ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱም የመንግስት አካላት ተወካዮች፤ የተለያዩ ተቋማት እና የማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ምሁራንና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
ስለሆነም የክልሉ ነዋሪዎች ከነገ ጀምሮ ለሚካሄደው የምክክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጡ ሂደት ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
በሌላ በኩል በቀጣይ ሳምንት በአማራ ክልል የአስተባባሪዎች ስልጠና እንደሚሰጥም ኮሚሽነሮቹ አመላክተዋል።
ይህንን በማድረግም በሁሉም ክልሎች መሰል ተግባሩን በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም ኮሚሽነሮቹ አንስተዋል።
በይስማው አደራው