አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የፋሲል አቢያተ መንግስት የጥገና ሂደትን እየጎበኙ ነው።
ሚኒስትሯ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችንም ተመልክተዋል።
በዚሁ ወቅት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ÷ በጎንደር አብያተ መንግስት የተጀመረው የጥገና ስራ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን በመግለጽ ቅርሱም ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ ከተሞች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ከጎንደር በተጨማሪ በጅማና በሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎችም የጥገና ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ሀብቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የመጠገንና የመጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው በበኩላቸው ÷ የፋሲል አብያተ መንግስት በአንድ ወቅት መጠነኛ ጥገና ተደርጎለት እንደነበር አንስተው አሁን ላይ ግን ዘላቂ የሚባል ጥገና በፌደራል መንግስት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከ1 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም በቅርሱ የጥገና ሂደት የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ገልጸው÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለጎንደር ከተማ ህዝብ እያደረጉ ላለው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በምናለ አየነው