አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ያስገነባውን የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ማዕከልና የመኖሪያ ቤቶችን አስመርቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሀይ ጳውሎስ በፕሮጀክቱ የተገነቡ ህንጻዎችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በመርሐ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ፣የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አቶ ረሻድ ከማል÷ለምረቃ የበቁት ህንጻዎች ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው÷ግንባታው በከፍተኛ ጥራት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ተገንብተዋል ነው ያሉት፡፡
የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ማዕከሉ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን÷ 1 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑ ተመላክቷል።
ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችና ማሽነሪዎች የተገጠሙለት ፋብሪካው 200 ሜኩ የኮንክሪት ውህድ በሰዓት የማምረት አቅም ያላው መሆኑም ተጠቁሟል።
ማዕከሉ 14 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን÷ ከዚህ ቀደም ተበታትነው ይገኙ የነበሩ የኮርፖሬሽኑን የእንጨት፣ የብረት፣ የመስታወት፣ የአልሙኒየም እና የሊፍት ወርክሾፖችን ወደዚህ ማዕከል እንዲገቡ ተደርጓል ነው የተባለው።
አስተማማኝ የጥሬ እቃ አቅርቦቱ እንዲኖር የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተመላክቷል።
በመራኦል ከድር