አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አካባቢ ትናንት ምሽት የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በድጋሚ መከሰቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ ሕዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
በዩኒቨርሲቲው የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ሃላፊ አታላይ አየለ (ፕ/ር) እንዳሉት፥ በአዋሽ ፋንታሌ ወረዳና አካባቢው ከትናንት ቀን ጀምሮ የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል።
ከሌሊቱ 6:13 ላይም የዕለቱ ከፍተኛው በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 6 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረትም አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ድረስ መሰማቱን ነው የገለጹት።
በአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን ጠቁመው፥ ይሁን እንጂ መጠኑ አነስተኛ ስለሆነ ስጋት እንደማይሆን አስረድተዋል።
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ጥናት ትምህርት ክፍል ሃላፊ ጌታቸው ገብረጻዲቅ በበኩላቸው፥አዋሽ ፈንታሌ የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢው ካለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል ይኑረው አይኑረው የሚለውን መገመት እንደሚያስቸግር አብራርተዋል።
ለአካባቢው ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በመላኩ ገድፍ