አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪክስ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ የሚመካከርና የጋራ አቋም የሚይዝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም የመሩት ‘በብሪክስ+ ማዕቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና’ በሚል ርዕስ የክብ ጠረጴዛ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተሳትፈዋል።
የውይይቱ ትኩረት ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድን አባል ለምን ሆነች፣ ምን ጠቀሜታ አለው እንዲሁም ከኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ እና ፍላጎት ጋር እንዴት ይጣጣማል በሚለው ላይ እንደሆነ ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ብሪክስ የጋራ ዕይታ ያላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ፣ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ያሉ ሀገራት ስብስብ ሆኖ የተጀመረ እንደሆነ አስታውሰዋል።
ብሪክስ በተለያዩ የትኩረት መስኮች ትብብር የሚደረግበት ስብስብ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፖለቲካና የደህንነት፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ አመልክተዋል።
በፍጥነት በማደግ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የሚያስፈልጋትን ቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ ድጋፍና ኢንቨስትመንት ለማግኘት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ብሪክስ ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ የሚመካከርና የጋራ አቋም የሚይዝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ምን መምሰል እንዳለበት፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ይበልጥ አካታችና ፍትሃዊ እንዲሆኑ እንዲሁም የታዳጊ ሀገራትን ፍላጎት የሚያመላክቱ ጉዳዮች ላይ ብሪክስ አቋም ይዞ እንደሚሞግትም በአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ አባል መሆኗ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅና የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ድምጽ የመሆን ባህሏን ለማስቀጠል እንደሚያስችላት ተናግረዋል።