Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቀናቶች የቀሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከአራት ቀናት በኋላ ይደረጋል፡፡

በፈረንጆቹ ህዳር 5 ቀን 2024 የሚከናወነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አከራክሮ እና አነታርኮ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ አሜሪካውያንም ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚመራቸውን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በምርጫው ሂደት ቀድሞው የዴሞክራት ፓርቲ ተወካይ እና የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት ክርክር ቦታውን በሚመጥን ደረጃ ሙግት እንዳላደረጉ ግምት ስለተወሰደባቸው እንዲሁም በዕድሜ እና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ከእጩነታቸው በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

እሳቸውን በመተካት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሀሪስ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ በመሆን የምርጫ ቅስቀሳዎችን ሲያናውኑ ቆይተዋል፡፡

ሪፐብሊካንን በመወከል ደግሞ ከስምንት ዓመታት በፊት የዲሞክራት ዕጩ የነበሩትን ሂላሪ ከሊንተንን በማሸነፍ አሜሪካን ከፈረንጆቹ 2017 እስከ 2020 ድረስ በፕሬዚዳንትነት የመሯት ዶናልድ ትራምፕ በዕጩነት ይወዳደራሉ፡፡

አወዛጋቢው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፣ በውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት፣ ታክስ ማጭበርበር እና ፆታዊ ትንኮሳዎች የሚሉ የክስ ዶሴዎችን በመዝጋት ነው ዳግም አሜሪካን ለመምራት እየተፎካከሩ የሚገኙት።

የ78 ዓመት አዛውንቱ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ በነበሩበት ወቅት እና በመደበኛ የህይዎት እንቅስቃሴያቸው ወቅት ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በእስራኤል-ጋዛ-ሂዝቦላህ እና ኢራን፣ በሩሲያ እና ዩክሬን፣ በሱዳን ጦርነት፣ በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ባለው ውጥረት ዋሽንግተን ስለሚኖራት ሚና የሚነሱ ፈታኝ ጥያቄዎችን ያረገዘ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የስደተኞች ጉዳይ፣ የአሜሪካ ኢኮኖሚ፣ የግለሰብ ነፃነት እና እምነት፣ የአየር ንብረት እና አካባቢ ጥበቃ፣ ታክስ እና የንግድ ልውውጥ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ትኩረት የተሰጠባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡

አሜሪካ በምትከተለው ኢሌክቶራል ኮሌጅ ስርዓት መሰረት ካማላ ሀሪስ ወይም ዶናልድ ትራምፕ ቢያንስ 270 ኢሌክቶራል ኮሌጅ ማግኘት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ውጤቱ በሚቀጥለው ማክሰኞ በይፋ የሚታወቅ ይሆናል፡፡

Exit mobile version