አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “የህልም ጉልበት፤ ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት 10 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ 3ኛ ዙር የአመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ ተጠናቀቀ።
አመራሩ በንድፈ ሀሳብና በነባራዊ እውነታዎች ተደግፎ ያገኘውን ስልጠና ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በመቃኘት በየደረጃው ህዝቡ ያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ እንደሚያስችል ተገልጿል።
ስልጠናው የተገኙ ልምዶችን ማስፋት የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል።
አመራሩ የትናት ወረቶችን እና የዛሬ አቅሞችን በውል በመለየት ህልሞችን ወደ ተጨባጭ እውነታዎች ለመቀየር የሚያስፈልገው የተስፋ ስንቅና ጉልበት ጨብጦ በሚመሩት ተቋማት እመርታዊ ውጤት ለማስመዝገብ ተጨማሪ አቅም የሚያጎለብትና መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተሰጠው ስልጠና የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በመፍጠር የኅብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል አመራሩ የመሪነቱን ሚናውን በሚገባ በመወጣት ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ለማሳካት ያስችላል ተብሏል።
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዙሮች ያካሄዳቸውን የአመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና በስኬት ማጠናቀቁን የፓርቲው መረጃ አስታውሷል።