Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከደረጃ በታች የሚያመርቱ 14 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥራት ደረጃ በታች ምርት በሚያመርቱ 14 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ 100 ፋብሪካዎች ላይ የኢንስፔክሽን ስራ ተሰርቷል።

በዚህም የ14 ፋብሪካ ምርቶች ከጥራት ደረጃ በታች ሆኖ በመገኘታቸው ርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጿል።

እርምጃ የተወሰደባቸው ፋብሪካዎች የቆርቆሮ፣ የዕቃና የልብስ ሳሙናዎች፣ የአርማታ ብረት፣ ዱቄት ሳሙና፣ ዋየር፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ ማከፋፈያ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህም ድርጅቶቹ ከማምረት ሂደት እንዲታገዱ፣ ምርትን ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ የማሸግ ስራ እንዲሁም ምርታቸውን ከገበያ ላይ እንዲሰበስቡና የማስተካከያ ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያደርግ እርምጃ ተወስዷል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከደረጃ በታች በሆኑ 3 ሺህ ካርቶን የልብስ ሳሙና፣ 543 ፍሬ ፈሳሽ የዕቃ ማጠቢያ ሳሙናዎች፣ የአሌክትሪክ ገመዶች እና 2 ሺህ 683 ባለ 14 ዲያሜትር አርማታ ብረት ወደ ገበያ እንዳይወጣና እንዲወገድ መደረጉ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም 77 ሺህ 356  ሽንሽን ቆርቆሮ ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ የማድረግ እና 760 ጥቅል የተለያየ መጠን ያላቸው ዋየር ምርቶች ለገበያ እንዳይቀርቡና ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ በማደረግ አስተዳደራዊ  እርምጃ ተወስዷል፡፡

በዚህም ሸማቹ ንጥራታቸውና ደህንነታቸው ካልተረጋገጡ ምርቶች በመከላከል የማህበረሰቡን ጤናና ደህንነት ማስጠበቅ መቻሉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version