ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሰሜን ኮሪያ እስከ አሜሪካ ሊደርስ እንደሚችል የተነገረለት ሚሳዔል ሞከረች

By Feven Bishaw

November 01, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ ሀዋሶንግ-19 የተባለ አህጉር አቋራጭ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባላስቲክ ሚሳኤል ትናንት መሞከሯን አስታወቀች፡፡

ሀዋሶንግ-19 7 ሺህ 687 ኪሎ ሜትር ርቀት በ86 ደቂቃ ውስጥ መጓዙ የተነገረ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ሙከራ ሀገሪቱ ስታደርግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ሙከራው በመደበኛ መንገድ ቢከናወን 15 ሺህ ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ እንደሚችል ተነግሯል።

ይህም ማለት ከደቡብ ኮሪያ አሜሪካ ለመድረስ እንደሚችል ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ሙከራውን ያደረገችው አቅሟ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት ታስቦ እንደሆነም ተነግሯል።

እንዲሁም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ሩሲያ መላካቸውን ተከትሎ ከተሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለተንጸባረቁ ሃሳቦች ምላሽ ለመስጠት ታስቦ የተደረገ ሳይሆን እንዳልቀረ ኮሪያ ጆንግአንግ ዴይሊ ዘግቧል።

የሚሳዔል ሙከራው ሲከናወን የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከልጃቸው ጁ አኢ ጋር ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል።

በባላስቲክ ሚሳዔል ሙከራ ሂደቱ የተደሰቱት ኪም ጆንግ ኡን፤ ሙከራው ሰሜን ኮሪያ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሀያል ሀገር መሆኗን ለዓለም ህዝብ ዳግም ያረጋገጠችበት ነው ብለዋል፡፡