የሀገር ውስጥ ዜና

እየተተገበረ ያለውን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የበለጠ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተመላከተ

By Feven Bishaw

November 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለውን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የበለጠ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በ2017 ዓ.ም የ100 ቀናት የሪፎርም እና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸሞች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ÷ የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አመርቂ ስኬቶችን ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።

የተደረገው ማሻሻያ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የተሻሻለ የመንግሥት ገቢና ኢንቨስትመንት፣ የቀነሰ የመንግሥት ዕዳ ጫና፣ ተወዳዳሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ያደገ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ስኬት እንደተመዘገገበት አንስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው÷ ማሻሻያው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከቀጣናው ከአሕጉሩ እና ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር የበለጠ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የበለጠ ለማስተዋወቅ መሥራት እንደሚገባ መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ባሉበት ኢኮኖሚው እያደገ መሄዱ ትልቁ የማሻሻያው እርምጃው ስኬት መሆኑንም ገልጸዋል።