አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ስሎቪኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ እና የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር ታንያ ፋጆን አረጋገጡ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከታንያ ፋጆን ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መፍጠሩን ያስረዱት ጌዲዮን (ዶ/ር)÷ የስሎቬኒያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከስሎቬኒያ ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር በተለይም በግብርና እና በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ኢትዮጵያ ትብብሯን ማጠናከር እንደምትፈልግ ማስረዳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ጉልህ ሚናም አብራርተዋል፡፡
በድኅረ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል (አትሚስ) የኃይል ስምሪት ውሳኔ፣ ሂደት እና አተገባበር ላይ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣናው አሸባሪው አልሸባብን በመዋጋት ረገድ የኢትዮጵያ ሚና የማይተካ እንደነበር አውስተው÷ የተገኙ ድሎች እንዳይቀለበሱ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጋር በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ታንያ ፋጆን በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መሥኮች በጋራ አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በውኃ አጠቃቀም፣ በግብርና መስክ በንብ ማነብ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ያላትን ልምድ እናተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ አዲስ የተከፈተውን የስሎቬኒያ ኤምባሲ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል፡፡