Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመሬት መንሸራተት የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮንታ እና ካፋ ዞኖች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በክልሉ ኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ጫሬ ዶቄ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሥድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

በቀበሌው ትናንት ምሽት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ዛሬ ጠዋት 2 ሠዓት ላይ የመሬት መንሸራተት መከሰቱንም አስረድተዋል፡፡

በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች የሁለት ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ÷ ከአንደኛው ቤተሰብ አራት እንዲሁም ከሌላኛው ቤተሰብ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ አብራርተዋል፡፡

በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋም ሁለት ቤት መውደሙን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል፡፡

የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው÷ እስከ አሁን 5 አስከሬን ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በአካባቢው አሁንም መሬቱ እየተናደ መሆኑ እና የውኃ ሙላት (ጎርፍ) መኖሩ የነፍስ አድን ሥራውን በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ በክልሉ ካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ ግራዋ ሽሽማ ቀበሌ በጣለው ከባድ ዝናብ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው ማለፉን ነው የገለጹት፡፡

ይህ አደጋ ዛሬ ከረፋዱ 4 ሠዓት ላይ መከሰቱን እና አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንዳሉ ሕይወታቸው ማለፉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህኛው አደጋም በሁለት መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version