የሀገር ውስጥ ዜና

ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ

By Feven Bishaw

November 01, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የሩብ ዓመቱን አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በሰብል ከተሸፈነው 20 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ያለው ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ አርሶ አደሩ በርብርብ ሰብሉን እንዲሰበስብም አስገንዝበዋል።

የመኽር ሰብል ቀድሞ በተሰበሰበባቸው ቆላማ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ ስራ መጀመሩንም ጠቅሰው፤ የበጋ መስኖ ስራ የተጀመረባቸው ክልሎች ኦሮሚያና አማራ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተያዘው ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱንም አንስተው፤ በዚህም እስካሁን 805 ሺህ ሄክታር መሬት ዝግጁ መደረጉን ተናግረዋል።

ከዚህም መካከል 505 ሺህ ሄክታር ያህሉ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በ2017/18 ምርት ዘመን 24 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት መታቀዱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ሐምሌ 2016 ዓ.ም ላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሂደት መጀመሩን አስታውሰው፤ ከጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም በፊት የመጀመሪያዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ እንደምትደርስ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም 2 ሚሊየን ኩንታል የተለያዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በ2016/17 የምርት ዘመን 30 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል በሆልቲካልቸር እና በጥጥ በመሸፈን 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

በመሳፍንት እያዩ እና ታሪኩ ወ/ሰንበት