አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የባለድርሻ አካላት ምክክር ተጀመረ።
በመድረኩ የመንግስት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ከማህበረሰብ ክፍል የተወከሉ ተሳታፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ተገኝወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ በችግርም ይሁን በደስታ አብሮ የመቆም እሴት ያለባት ሀገር ናት ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀሳብ ልዩነቶች ወደ አለመግባባት እየሄዱ ችግሮች እየተፈጠሩ እንደሆነ ጠቅሰው÷ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እነዚህን አለመግባባቶች በምክክር ለመፍታት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አሁን ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኩ ቀደም ሲል ከማህበረሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማካተት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚጠናከሩበትም ይሆናል ተብሏል።
ምክክሩ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ የባለድርሻ አካለት ተወካዮችም የሚመረጡ ይሆናል።
በዘመን በየነ እና ኢብራሂም ባዲ