የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ለማጠናከር በቅንጅት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

November 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር በጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር መንቀሳቀስ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡

ሚኒስትሩ በመላው ዓለም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር በጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር መቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ወቅታዊውን የዓለም ጂኦ-ፖለቲካ አካሄድ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትጋት እንደሚንቀሳቀሱ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡