አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፥ ባንኮች እርስ በርሳቸው የሚበዳደሩበት የገንዘብ ገበያን ይፋ አድርጓል፡፡
ብሔራዊ ባንኩ ባወጣው መግለጫ ÷ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይት መጀመሩ የብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በማጠናከር እና ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣም ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
ይህ ጅምር ባንኮች በባንክ ሥርዓቱ ውስጥ የገንዘብ ፍሰትን በብቃት እንዲያስተዳድሩ ይረዳል፤ እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ በአጭር ጊዜ የወለድ ተመን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ያስችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፥ ባንኮች እርስ በርሳቸው የሚበዳደሩበት የገንዘብ ገቢያ ይፋ አደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወለድ ተመንን መሰረት ወደአደረገ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መግባቱን ተከትሎና በመካከለኛ ጊዜ ስትራቴጂ ዕቅዱ ሲተገበራቸው ከያዛቸው ዕቅዶች አንዱ የሆነው በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት እንዲጀመርና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ኃላፊነት ወስዶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ይህንንም ለማሳካት ባንኩ እንደ ተቆጣጣሪ አካልነቱ መመሪያና የሥነምግባር ደንብ በማውጣትና ባንኮች እርስ በርሳቸው ለሚያደርጉት የገንዘብ ግብይት የሚጠቀሙበትን የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ሥርዓት በማፅደቅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ገበያን መጀመር ፥ ንግድ ባንኮች የዕለት-ተዕለት የገንዘብ ፍሰታቸውን በአግባቡ እንዲያስተዳደሩ ያግዛል ፤ የባንክ ዘርፉን ለማጠናከር ይረዳል ፤ በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት የአጭር ጊዜ ማለትም የአንድ ቀን ወይንም የሰባት ቀናት የመክፈያ ጊዜ ያላቸው ብድሮች ያካትታል። ይህም ባንኮች የአጭር ጊዜ የገንዘብ ጉድለትን በመሸፈን ወይም ትርፍ ገንዘብን ለሌሎች ባንኮች በማበደር የገንዘብ ፍሰትን በብቃት እንዲያስተዳደሩ ያስችላቸዋል።
ባንኮች ያላቸውን ገንዘብ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያደርጋል፤ በባንኮች መካከል ጤናማ ውድድርን በመፍጠር ዘመናዊ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይትን ለማዳበር፣ በአጠቃላይ የገበያ መረጋጋትን ለማሻሻል ይረዳል ፤ የገንዘብ እጥረት ስጋትን በመቀነስ እና በተረጋጋ የወለድ ተመን ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።
ውጤታማ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ በመደገፍ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ማሻሻያ ለማጎልበት ያግዛል፡፡
በመሆኑም ይህ ጅምር ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን እና በባንኮች መካከል የሚደረግን ግብይት ለማገዝ ከሚያደርገው ጥረት ጋር የተጣጣመ ነው።
ከላይ የተገለፁትን ጨምሮ የገንዘብ ገበያውን እውን ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የተጠናቀቁ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንኮች መካከል የሚደረግን የገንዘብ ግብይት መጀመር ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህም የገንዘብ ገበያ የወለድ ተመንን መሠረት ያደረገውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ትግበራ ለማጠናከር እና በባንክ ዘርፉ ውስጥ የሚገኝ ገንዘብን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀምና ለማስተዳደር የሚያስችሉ የሚከተሉትን እርምጃዎች ያጠቃልላል፡-
• አንደኛ ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት በይፋ መጀመሩን እና ንግድ ባንኮች የአጭር ጊዜ ማለትም ለአንድ ቀን ወይም ለሰባት ቀናት መቆየት የሚችል ገንዘብ መበደርና ማበደር የሚችሉ መሆናቸውን ያበስራል፡፡ ይህም በባንክ ዘርፉ ያለውን የገንዘብ ፍሰት አስተዳደርን በማጎልበት እና የፋይናንስ ዘርፍን ለማረጋጋት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው። በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት ለባንኮች አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ግልጽነት ያለው የዕለት ተዕለት የገንዘብ ፍሰት ፍላጎቶቻቸውን የሚያስተዳድሩበትን ምቹ ምህዳር ይፈጥራል፤ በባንኮች መካከል ትብብር እንዲኖርና የገንዘብ ፍሰት እንዲዳብር ያደርጋል ፤
• ሁለተኛ፡- በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የግብይት መድረክ ላይ ብቻ እንዲሆን ብሔራዊ ባንክ ፈቅዷል።
ይህም የሆነበት ምክንያት የሰነደ ሙዓለ ንዋይ የግብይት ሥርዓት መድረክ ከፍተኛ የደህንነት፣ የቅልጥፍና፣ የግልጽነት እና ጥሩ የሆነ የግብይት የሪፖርት አቀራረብን ያረጋገጠ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የተፈቀደው የግብይት መድረክ በባንኮች መካከል የሚደረጉ የገንዘብ ግብይቶችን በማቀላጠፍ እና ለገንዘብ ፍሰት አስተዳደር ወጥ የሆነ የገበያ ቦታ በመመሥረት ሁሉም የንግድ ባንኮች ወሳኝ የሆኑ የገንዘብ ሃብቶችን በገበያው ላይ በእኩልነት እንዲገበያዩ ያስችላል፡፡
▪️ ሦስተኛ ፡- በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የገንዘብ ገበያ መመሪያ እና የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ይከናወናል፡፡ የቁጥጥር መመሪያዎች ሁሉም ተሳታፊ ባንኮች ሕግና ደንቦችን እንዲሁም የአሰራር መርሆችን እንዲያከብሩ ያደርጋል ፤ በገበያ ውስጥ ግልፅነትን፣ ፍትሃዊነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን በባንኮች መካከል በሚደረጉ ግብይቶች ላይ መተማመንን ይፈጥራል፡፡
▪️ አራተኛ ፡- በባንኮች መካከል በሚደረግ የገንዘብ ግብይት ለመሳተፍ ሁሉም የንግድ ባንኮች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ማግኘት እና የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማሟላት አለባቸው፡፡ ይህም ማለት በገበያው ውስጥ መሳተፍየሚችሉት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሳተፉ ፍቃድ የተሰጣቸው የንግድ ባንኮች ብቻ ይሆናሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት ታማኝነት እና ተጠያቂነትን በማስፈን የገበያ መረጋጋትን ለማሰጠበቅ ነው፡፡ ይህም ሁሉም ባንኮች የሚፈፅሟቸው ግብይቶች ተገቢው የአሠራር ሥርዓት የተከተሉ እንዲሆኑ ያደርጋል።
▪️ አምስተኛ ፡- በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት የወለድ ተመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የፖሊሲ የወለድ-ተመን ክልል ውስጥ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ይህም ማለት ይህ የወለድ ተመን ክልል የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ተመንን መሠረት ያደረገ ሆኖ ከዚህ የፖሊሲ የወለድ ተመን በ3 በመቶ ከፍ ወይም በ3 በመቶ ዝቅ ሊል የሚችል ነው፡፡ የፖሊሲ የወለድ ተመን ወለል መቀመጡም በባንኮች መካከል የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች ሊገመት በሚችል መልኩ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በባንኮች መካከል የሚደረገው የገንዘብ ግብይት የወለድ ተመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የወለድ ተመን (NBR) ጋር ሳይጣጣም የቀረ እንደሆነ የገንዘብ ፍሰት አስተዳደር ስልቶችን በመጠቀም አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡
▪️ ሥድስተኛ ፡- ሁሉም ንግድ ባንኮች በባንኮች መካከል በሚደረግ የገንዘብ ግብይት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና አዲሱን የንግድ መድረክ እንዲጠቀሙ ብሔራዊ ባንክ ምክሩን ይለግሳል፡፡ ይህ በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት የባንክ ዘርፉን በማጠናከር ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም በኢኮኖሚው ዉስጥ ቀልጣፋ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖርና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፋጠን ይረዳል፡፡
ማጠቃለያ
የባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይት መጀመሩ የብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በማጠናከር እና ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣም ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይህ ጅምር ባንኮች በባንክ ሥርዓቱ ውስጥ የገንዘብ ፍሰትን በብቃት እንዲያስተዳድሩ ይረዳል፤ እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ በአጭር ጊዜ የወለድ ተመን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ያስችለዋል፡፡
በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት የወለድ ተመን ከተቀመጠው የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ተመን ክልል ውጭ ሲሆን ፥ ብሔራዊ ባንክ የብድር እና የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት በማቅረብ ወደ ተፈቀደው የወለድ ተመን ክልል እንዲመለስ ለማድረግ ጣልቃ ይገባል፡፡
በመጨረሻም በባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይት የሚሳተፉ ሁሉም የንግድ ባንኮች ለጋራ ተጠቃሚነት እንዲሠሩ፣ የብሔራዊ ባንክን መመሪያዎችና የአሠራር ደንቦችን እንዲያከብሩና በገበያ ተሳታፊዎች መካከል ሙሉ ትብብር እንዲኖርየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥሪውን ያቀርባል፡፡