የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ያሉ የመንገድ ልማት ስራዎች ለኢንቨስትመንት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው – ወ/ሮ አለሚቱ

By amele Demisew

October 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)በክልሉ እየተሰሩ የሚገኙ የመንገድ ልማት ስራዎች ለኢንቨስትመንት እድገት አስተዋጽዖቸው የጎላ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡሙድ ገለጹ፡፡

ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማት አውታሮችን ጎብኝተዋል።

ከተጎበኙት ውስጥ ከጋምቤላ -አበቦ -ፒኝውዶ አስፋልት መንገድ ስራ ፕሮጀክት ፣ ከፒኝውዶ ወደ ጊሎ ወንዝ የሚያደርሰው አስፋልት መንገድ እና በጊሎ ወንዝ ላይ እየተሰራ የሚገኘው ድልድይ ይገኙበታል።

ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት÷ በፌደራል መንግስት በክልሉ እየተሰሩ የሚገኙ የመንገድ ዝርጋታዎች ለክልሉ የኢንቨስትመንት እድገት እንዲሁም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ሚናቸው የጎላ ነው።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መንገዶች እየተሰሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የቆሙ እና የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸው አንስተው ዛሬ የጎበኟቸው ፕሮጀክቶች ግን የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ክልሉ ለኢንቨስትመንት አመቺ እና ሰላም የተረጋገጠበት በመሆኑ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሀብቶችን የክልሉ መንግስት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።