Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አማራ ክልልን ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ወደነበረበት ለመመለስ የክልሉ ተቋማትና የሥራ ሃላፊዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

“ሠላም ለሁሉም፣ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሃሳብ ከክልሉ ተቋማት ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች ጋር የሠላም ኮንፈረንስ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል፡፡

በኮንፈረሱ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና ርዕዮት ዓለም ዘርፍ ሃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)÷የሠላም ትርጉሙ የሚታወቀው ሠላም ሲደፈርስ መሆኑን በመጥቀስ ይህንንም በክልሉ ባለፈው አንድ ዓመት በተግባር አይተነዋል ብለዋል፡፡

ሠላም ለሰው ልጆች ፍላጎት መሻት ዋስትና በመሆኑ ከምንተነፍሰው አየር ባልተናነሰ ሁኔታ ከፍ ያለ ዋጋ አለው ነው ያሉት፡፡

ግጭት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና፣ በማህበራዊ መስኮች እጅግ አደገኛ ጥፋትን ያስከትላል፤ ግጭት ሰውና ሀብትን ከማውደሙ በተጨማሪ በትውልዶች መካከል ከፍተኛ ክፍተትን ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ካለው የግጭት አዙሪት ለመውጣት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸው÷ በሁሉም ቦታዎች ውጤታማ ስራ መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

የሰላም ኮንፈረንሱ በክልል ደረጃ መካሄዱ ዋና አላማ በባለፈው ዓመት የመጣንባቸውን ምዕራፎች በጥልቀት በመገምገም ሰላምን በክልሉ የማረጋገጥ ስራ በማጠናከር ሚናችንን እንደየሃላፊነታችን ለመወጣት ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የባሕርዳሩን መድረክ ጨምሮ 41 የሰላም ኮንፈረስ መድረኮች እንደሚካሄዱ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version