አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን መንግስት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ሕይዎታቸው ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጀንስ ሃነፌልድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም አቶ ተመስገን የቀደሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ሕይዎታቸው ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክተው ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በትግራይ ክልል የመጀመሪያ ዙር መስፈርቱን የሚያሟሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ እንደሚጀመር አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የጀርመን መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት እየተገበረ ያለውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ሥራቸው የመመለስ ፕሮግራም እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ጀንስ ሃነፌልድ በበኩላቸው ÷የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አድንቀዋል፡፡
ለቀድሞ ተዋጊዎች መልሶ የማቋቋም ፕሮግራም ስኬትም የጀርመን መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡