የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ -ክፍል ሁለት

By ዮሐንስ ደርበው

October 31, 2024

– ሰላምና ደህንነትን በተመለከተ

 

ከማንም በላይ ሰላም እንፈልጋለን፡፡ ጦርነትን በተግባር እናውቀዋለን፤ አንፈልገውም፡፡ ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሰላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛ ነው፡፡ መንግስት ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ ሰርቷል፡፡ አሁንም ያለን አቋም የትኛውም አይነት አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ነው፡፡ ነገር ግን የትኛውም አካል በኃይል እና ጥላቻ መጠፋፋትን እንጂ ዓላማውን ማሳካት አይችልም፡፡ ሰከን ብሎ ማሳብ ይገባል፡፡ ሃሳብ አልባ ትግል ፍሬ የለውም፡፡

– የአማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ

በአማራ ክልል ላይ ከየትኛውም መንግስት በላይ አሁን ያለው መንግስት በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በክልሉ ታላላቅ የመንገድ፣ የኢንዱስትሪ የቱሪዝም ልማቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ በዚህም ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ የፋሲል ቤተ-መንግስት እየታደሰ ነው፤ በዋና ዋና ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው፡፡ የመገጭ ግድብን 7 ቢሊዩን ብር መድበን ከበርካታ ዓመታት የግንባታ መቋረጥ በኋላ ቀን ከሌት እየገነባን ነው፡፡ ነገር ግን በክልሉ ልማት እንዳይከናወን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች አሉ፡፡ ይህን ተባብረን ማስቆም አለብን፡፡ የአማራ ህዝብ ማን እንደሚሰራለትና ማን እንደሚያወራለት ጠንቅቆ የሚያውቅ ጨዋ ህዝብ ነው፡፡ መንግስት ክልሉን የማልማት ስራውን አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

– የገዥ ትርክት ውቅሮች

ህገመንግስታዊነት

የህግ መንግስት መርሆችና ዴሞክራሲን ያከበረ የጋራ ትርክት መገንባት

ህብረብሔራዊነት

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር፣ብሔረሰብና ህዘቦች ሀገር መሆኗን መቀበል ያስፈልጋል፡፡

ብልጽግናን በየደረጃው ማረጋገጥ

በሁለም አግባብ በየደረጃው ልማትና ብልጽግናን በማረጋገጥ ድህነትን ለመድፈቅ በጋራ መስራት ይገባል፡፡

ማረምና ማስቀጠል

ትናንት የነበሩ ድክመቶችን ማረም፤ ያሉ ጥንካሬና ወረቶችን ደግሞ ማስቀጠል ይገባል፡፡

ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር

የጋራ ህልም በመፈጠር የበለጸገችና ያደገች ኢትዮጵያን ለማየት በጋራ መሰለፍ ይገባል፡፡ ከፓርቲ ባለፈ ትውልድን የሚሻገር እሳቤ መፍጠር ይገባል፡፡

– ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በተመለከተ

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሻለ ስኬት እንዲያስመዘግበ የምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ለታሃድሶ ኮሚሽንን እና ለሽግግር ፍትህም መሰል ድጋፍ መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ኮሚሽኖች ትምህርት በመውሰድ አሁን ያሉ እድሎችን መጠቀም ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስት እንደ አስፈጻሚ አካል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

– ኮሪደር ልማትን በተመለከተ

ኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው፡፡ ከከተሜነት እድገት ጋር የተሳሳረ ልማት ነው፡፡ በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መንገድ ከመስራት ባለፈ ታዳጊዎች እግር ኳስ የሚጫወቱባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የእግረኛ መንገዶች ተሰርተዋል፡፡ ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማት ለዜጎቻችን ያቀረብንበት ነው፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች ከምንሰራው የኮሪደር ልማት ባሻገር፤ የገጠር ኮሪደር ልማት ጀምረናል፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ኑሮ ይገባቸዋል በሚል የተጀመረ ነው፡፡ የተሟላ ብልጽግናን የምናረጋግጠውም በዚሁ መንገድ ነው፡፡

– ዲፕሎማሲን በሚመለከት

የኢትዮጵያ አቋም ከሁሉም ጋር በትብብርና ሰጥቶ በመቀበል መርህ መኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኃይል ማዕከል ናት፤ ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ልማት ቁርጠኛ ናት፡፡ ከየትኛውም ጎራ ጋር ሳንሰለፍ ከሁሉም ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ለብሔራዊ ጥቅማችን እንሰራለን፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን በመገንዘብ ሀገርን አስቀድሞ መስራት አለበት፡፡ በውስጥ የሚኖረን አንድነትና ሰላም ለዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬያችን ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

– የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ

ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባህር ላይ የባህር በር ያስፈልጋታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ወደ ኋላ የማይል ይፋዊ አቋም አለን፡፡ ነገር ግን ይህን ለማሳካት ጦርነትም ሆነ የኃይል አማራጭ አንፈልግም፡፡ ፍላጎታችንን ማሳካት የምንሻው በሰላማዊ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ምክንያታዊና ፍትሃዊ ጥያቄ ነው፤ እኛ ባናሳካው ልጆቻችን ያሳኩታል፡፡ ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ላይ ወረራም ሆነ ጥቃት አትፈጽምም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሞክሩ ካሉ አሳፍረን እንመልሳለን፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስችል በቂ አቅም አለን፡፡

#የጠሚሩምላሾች

#PMOEthiopia