አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከሚያሳካ ማንኛውም ሀገር እና ተቋም ጋር በትብብር እንሰራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚከናወኑ አንስተዋል፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርሕ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት፣ በየነ መንግስታት እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡
ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት፣ ከብሪክስ አባል ሀገራት ከአፍሪካ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ግንኙነት እዳላት አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ጠቁመው÷ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከሚያሳካ ማንኛውም ሀገር እና ተቋማት ጋር በትብብር እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ነገር ግን ኢትዮጵያን በሃይል ለማንበርከክ የሚሞክሩ ሃይሎችን አንታገስም ብለዋል፡፡
ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ኢትዮጵያ መሬት እንደቀማች ተደርጋ እንድትታይ ለማድረግ መሞከሩን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ የስምምነቱን ይዘት በተመለከተ በርካታ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ማከናወኗን ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ በቀይ ባሕር ወደብ ያስፈልጋታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒትስትሩ ÷ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት እንደማይቀርም አስገንዝበዋል፡፡
ይህን በመገንዘብ የሶማሊያ መንግስት ኢትጵያን በተለያዩ ሀገራት በመዞር ከመክሰስ ይልቅ በቀጣናዊ ትብብር መንፈስ ሃሳቡን እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ