Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጅማሮ ሥራ ጥሩ የሚባል ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጅማሮ ሥራ ጥሩ የሚባል ነው ሲሉ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው፡፡

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ከፓርላማ አባላት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በሚመለከት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰጡት ምላሽ የምክክር ኮሚሽኑ ጅማሮ ስራ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአብዛኞዎቹ ቦታዎች ህዝቡን እያወያየና አጀንዳ እየለየ ይመስለኛል፤ በአንዳንድ ነገሮች እንደፈለግነው ባይፈጥነም ጅማሮው ጥሩ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚመራው በፓርላማ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚህም ኮሚሽኑ ለውጥ እንዲያመጣና የተሻለ ስኬት እንዲያስመዘግብ የምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠቁመዋል፡፡

መንግስትም እንደ አስፈጻሚ አካል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት፡፡

ከተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በተያያዘም በየቦታው የታጠቁ ሃይሎች አሉ፤ ታድሶ ኮሚሽኑ እንዳይሰራ እንቅፋት ከምንሆን ቶሎ አሳክተን ከክላሽ ይልቅ ሞፈርና ትራክተር እንዲይዙ አድርገን ብናሰራው ይሻላል ሲሉ መክረዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ እንዳያመልጠን መጠቀም ይገባል፤ በአጠቃላይ እንደ ምክክር ኮሚሽኑ ሁሉ ለተሃድሶ ኮሚሽን እና ለሽግግር ፍትሕም አስፈላጊው ድጋፍ መደረግ አለበት ነው ያሉት፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version