Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አሁን ላይ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሰላምና ደህንነትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ስለአማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታ ማብራያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በአማራ ክልል ከየትኛውም መንግስት በላይ አሁን ያለው መንግስት በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አማራ ክልልን የኢንዱስትሪ ማዕከል እናደርጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥በክልሉ ታላላቅ የመንገድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝምና ሌሎች ልማቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል፡፡

የፋሲል ቤተ-መንግስት እየታደሰ ነው፤ በዋና ዋና ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው ፤ የመገጭ ግድብን 7 ቢሊየን ብር መድበን ከበርካታ ዓመታት የግንባታ መቋረጥ በኋላ ቀን ከሌት እየገነባን ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን በክልሉ ልማት እንዳይከናወን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች እንዳሉ አንስተው ፥ ይህን ተባብረን ማስቆም አለብን ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ክልላችን ፤ የአማራ ህዝብ ህዝባችን ነው ፤ የምንቆጣጠረው የለም ፤ አብረን ነው የኖርነው ፤ አብረን ነው የታገልነው ፤ አብረን እንኖራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ህዝብ ማን እንደሚሰራለትና ማን እንደሚያወራለት ጠንቅቆ የሚያውቅ ጨዋ ህዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ መንግስት ክልሉን የማልማት ስራውን አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ካልለማና ካልተቀየረ ኢትዮጵያ አትቀየርም ፤ እኛ የአማራ ክልል በኢትዮጵያ ብልጽግና ውስጥ ያለውን ሚና አቅልለን የምናይ አይደለንም ብለዋል፡፡

በዚህም ክልሉ እንዲቀየር አግዙን ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈው ፤ የሚያደናቅፉን ሰዎች የልማት ጊዜውን እንዳያራዝሙት መተጋገዙ ይሻላል ብለዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

Exit mobile version