አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት አሁንም ያለው አቋም ግጭቶች እና አለመግባባቶች በሰላም እንዲፈቱ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሰላምና ደህንነትን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ፥ ሰላም ለሌሎች የልማት ሥራዎች አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር ንግግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ከማንም በላይ ሰላም እንፈልጋለን፤ ጦርነትን በተግባር እናውቀዋለን፤ አንፈልገውም ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሰላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ፥ መንግስት ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራቱን አብራርተዋል፡፡
አሁንም ያለን አቋም የትኛውም ዓይነት አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ሆኖም ግን የትኛውም አካል በኃይል እና ጥላቻ መጠፋፋትን እንጂ ዓላማውን ማሳካት አይችልም ብለዋል፡፡
ሃሳብ አልባ ትግል ፍሬ እንደሌለው አስገንዝበው ፥ ለዚህም ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አብረን እንስራ የሚል ጥሪ አቅርበው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በመሰረት አወቀ